Ethiopian Lutheran Church,  Mekane Yesus in Minneapolis (ELCA)

ሰማያዊ መና

 

                        ሰማያዊ መና 1

ንጉሡ ሄሮድስ ሰምቶ ደነገጠ እየሩሳሌምም ሁሉ ከእርሱ ጋር አብረው በድንጋጤ ታወኩ፡፡ ማቴዎስ 23

 

ንጉስ ሄሮድስ  ማንኛውም ነገር የተሳካለት የሚመስለው በጦርነት ጊዜም ከጦር ሜዳ በድል አድራጊነት የሚመለስ ኃይለኛ ንጉሥ ነበር፡፡ ሰዎችም ጠቢብ አስተዋይ ሀብታምና ገናና አድርገው ይገምቱት ነበር፡፡ ነገር ግን በውጫዊው ገፅታና አስተያየት ማንኛውም ነገር የቀናውና ደስተኛ መስሎት ቢታይ ዳሩ ግን ውስጡ ደስታና ሠላም ፈፅሞ የራቀውና ያልነበረው ሰው ነበር፡፡

 

የነገሥታት ንጉሥ የጌቶች ጌታ የሆነውን ክርስቶስን በሄሮድስ ምትክ ስንመለከተው ግን የተናቀና የተጠላ ሆኖ ይኖር ነበር፡፡ (መልክና ውበት የለውም ባየነውም ጊዜ እንወድደው ዘንድ ደም ግባት የለውም የተናቀ ከሰውም የተጠላ የሕማም ሰው ደዌንም የሚያውቅ ነው ሰውም ፊቱን እንደሚሰውርበት የተናቀ ነው እኛም አላከበርነውም፡፡ ኢሳያስ 533)

 

ኢየሱስ ግን በውስጡ ፍፁም ደስታ ሠላምና ተስፋ ከልቡ ተለይቶት አያውቅም ነበር፡፡ እኛም በበኩላችን በውጫዊው ደስታ የሚደለለው የዚህ ዓለም ሄሮድስ እውነተኛውን ንጉሥ ክርስቶስን እንዳይወስድብን እንጠንቀቅ፡፡ ምስኪንና ደኃ ሆኖ በግርግም ውስጥ ወደተኛው ሕፃን እንቅረብ፡፡ የነፍሳችንን ብፅዕና የምንፈልግ ከሆንን ንፁህና ተወቃሽ ባልሆነ ሕሊና መኖርን ከወደድን ሄሮድስን ትተን እውነተኛውን ንጉሥ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስን በሕይወታችን እንዲነግሥ እንፍቀድለት፡፡

 

በራሳችን መልካም ሥራና አምልኮ መታመናችንን መሐሪና ቸር የሆነውን ጌታ እየሱስ ክርስቶስን የልባችን ባለቤት እናድርገው፡፡

 

 

 

ሰማያዊ መና 2

ኮከቡንም ባዩ ጊዜ በታላቅ ደስታ እጅግ ደስ አላቸው፡፡ ወደ ቤትም ገብተው ሕፃኑን ከእናቱ ከማሪያም ጋር አዩት ወድቀው ሰገዱለት ሣጥኖቻቸውንም ከፍተው እጅ መንሻ ወርቅና ዕጣን ከርቤም አቀረቡለት፡፡ ማቴዎስ 210-11

 

 

ከምስራቅ አገር የመጡት ሰብዓ ሰገል ክርስቶስን ለማግኘት ሲሉ በመጀመሪያ በገዛ ሐሳባቸው ተመርተው ወደ እየሩሳሌም ሄደው አጡት፡፡ በኃላ ግን የነቢዩን የሚክያስን ቃል ልብ በማድረግ የራሳቸውን ሐሳብ ወደ ጎን ትተው ባደረጉትም ቅር ሳይሰኙ ቅድስቲቱንና የአገሩ ዋና ከተማ የሆነችውን እየሩሳሌምን ለቅቀው ወደ ታናሺቱና ወደ ተናቀችው ወደ ቤተልሔም  ጉዙአቸውን ቀጠሉ፡፡ ኮከቡም ሕፃኑ ወደ ነበረበት ቤት እስኪደርሱ ድረስ ብርሃኑን በመስጠት ይመራቸው ነበር፡፡

 

በኮከቡም መሪነት የደረሱበት ስፍራ እንዳሰቡት አልነበረም፡፡ ምክንያቱም ቦታው ለሰው ኑሮ ምቾት አልነበረውም፡፡ ሕፃኑም በግርግም ላይ ተኝቶአል፡፡ በቦታው ውኃ እንኳ አልነበረም፡፡ እንደዚህ ያለ ቦታ ለንጉሥ ብቁ ነው ለማለት አይቻልም፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎች የስፍራውን ወራዳነት ሳይመለከቱ የነቢዩን ቃል የኮከቡንም አመራር በመከተል በሕፃኑ ፊት ወድቀው ሰገዱለት እጅ መንሻውንም አቀረቡለት፡፡

 

እኛም የምስራቅ ጠቢባን ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን እንደፈለጉትና እንደሰገዱለት ልንፈልገውና ልንሰግድለት ይገባል፡፡ ስጦታቸውንም እንዳቀረቡለት እኛም ገንዘባችንንና ሀብታችንን ለመንግስቱ ማስፋፊያ በማዋል ልናገለግለው ይገባናል፡፡

 

                        ሰማያዊ መና 3

ከእነርሱም ጋር ወርዶ ወደ ናዝሬት መጣ፡ ይታዘዝላቸውም ነበር፡፡ ሉቃስ 251

 

በዚህ ቃል ወንጌላዊው ሉቃስ የክርስቶስን የወጣትነት ጊዜ ምን ይመስል እንደ ነበረ በፃፈው ውስጥ ያስተምረናል፡፡ ይታዘዝላቸው ነበር ሲል ምን ማለቱ ነው? መልሱም የሕጉን መፅሐፍ ስንመለከት ከአስርቱ ትዕዛዛት ውስጥ አራተኛውን ትዕዛዝ ይከተልና ይፈፅም ነበር ማለት ነው፡፡ በቤቱ ከእናቱና ከአባቱ እንደ ልጅ ትዕዛዝ እየተቀበለ በልዩ ልዩ ሥራ ያገለግላቸው ነበር ማለት ነው፡፡

 

እኛም የእርሱን መልካም አርአያ እየተከተልን ምንም ዝቅተኛና የተናቀ ሥራ ቢሆን ከእናት ከአባቶቻችን እንዲሁም በዕድሜ ከሚበልጡን የምንታዘዘውን ሥራ ብንፈፅም ለወላጆቻችንም ደስታ ሲሆን ለእኛም በረከት ነው፡፡

 

ክርስቶስ የሁሉ ጌታ ነው ቢሆንም ለአባቱና ለእናቱ እስኪታዘዝ ድረስ ራሱን ዝቅ አድርጎአል፡፡ ስለዚህ የእርሱ ታዛዥነት ለእኛ ትምህርት እንዲሆነን ያስፈልጋል፡፡

 

ከዚህ የምንማረው ነገር ቢኖር ክርስቶስ ወላጆቹ ሥራ ባዘዙት ቁጥር ራሱን ከፍ በማድረግ እንደዚህ ያለውን ሥራ መስራት ክብሬን ያዋርደዋል ብሎ አላሰበም በአይምሮውም ለአፍታ እንኳ አላሰላሰለም፡፡ ይህም ለእኛ መልካም አርአያ ሊሆነን ይገባል፡፡ እሺ ብትሉ ብትታዘዙ የምድርን በረከት ሁሉ ትበላላችሁ ተብሎ ተፅፏልና ነው፡፡

 

                       

ሰማያዊ መና 4

ስለ ምን ፈለጋችሁኝ በአባቴ ቤት እሆን ዘንድ እንዲገባኝ አላወቃችሁምን ሉቃስ 249  

 

እግዚአብሔር ሁሉን ነገር የፈጠረው ለእኛ ጥቅም እንዲሆን አድርጎ ነው፡፡ ማንኛውም ነገር ከእርሱ እየተቀበልን በምንፈልግበት ቦታ መንገድ ልናውለው እንችላለን፡፡ አምላካችን የራሱ ያደረገው አንድ ነገር አለ ይኽውም ቃሉን ነው፡፡

 

በቃሉ እግዚአብሔር በምዕማናን ልብ ውስጥ እየነገሠ ቅዱሳንና ብፁዓን ያደርጋቸዋል፡፡ ቤተ መቅደስ ማለት የእግዚአብሔር ቤት ማለት ነው፡፡ እንዲህም የተባለበት ምክኒያት ራሱን የሚገልጥበት ሕልውናውን የሚያኖርበትና ድምፁን የሚያሰማበት ቦታ ስለሆነ ነው፡፡

 

በዛሬ ጥቅሳችን ምሳሌነት ክርስቶስን የምናገኘው በሚያውቁትና በዘመዶቹ መካከል ሳይሆን የእግዚአብሔር ቃል በሚነገርበት ሥፍራ ነው፡፡ ምክኒያቱም እርሱ ዓለማዊ ወይንም ከዓለም ለመሆን ስለማይፈልግ ብቻ ነው፡፡

 

በዚህ ምድር ላይ በተመላለሰበት ዘመን እንደገለጠውና እንደተረከው ሁሉ አባቱ እግዚአብሔር በሚኖርበት መኖር ስለሚፈልግ ነው፡፡ እናቱ ቅድስት ማሪያምና ዮሴፍ ክርስቶስን በልዩ ልዩ ቦታ ፈልገው አጡት፡፡ ወደ እግዚአብሔር ቤት ብቻ ሲሔዱ ግን በዚያ በሥፍራው አገኙት፡፡

 

እኛም ብንሆን ክርስቶስን ቃሉ በሚነገርበት ቤተ መቅደስ መፈለግ አለብን፡፡ በዚህም ቦታ ሕብረትንና አንድነትን የሚወደውን ጌታ ፈልገን ስናገኘው ኃይል የሆነው ቃሉ ለፍሳችን የሚያረካና የሚያፅናና መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ ቀርቦም ሳለ ፈልጉት ተብሎ ተፅፏልና ነው፡፡ 

 

 

                        ሰማያዊ መና 5

 

                  አዘነላቸው፡፡ ማቴዎስ 14፡14

     

ይህ ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ ክብሩንና ሥልጣኑን ትቶ ከሰማይ ወርዶ ሥጋ ለብሶ እስከ መስቀል ሞት ድረስ የተዋረደበትን ዋና ምክኒያት ያስረዳል፡፡ ኢየሱስ ለጠፉት ያዝናል፡፡ ኢየሱስ እረኛ እንደሌላቸው በጎች ወዲህ ወዲያ ለሚንከራተቱት የሰው ልጆች ይራራል፡፡ እኛስ የጌታን አርአያውን ተከትለናልን? ቡዙዎቻችን ክርስቲያኖች በመባል የክርስቶስን ስም ተሸክመናል፡፡ ልባችን ለተቸገሩት ይራራልን? እጃችንስ ይዘረጋልን?

በዓለም ላይ ቡዙ መራብ  መጠማትና መራቆት አለ፡፡ በቡዙ የሚቆጠሩ ሰዎች በመንፈሳዊ ጨለማ ውስጥ ይኖራሉ፡፡ ቡዙዎቻችን ይህን አሳዛኝ ሁኔታ በዓይናችን ያየን ወይም ብሎም ሲነገር ሰምተናል ብዬ አምናለሁ፡፡ ታዲያስ የችግሮቻችን ሁኔታ ለማሻሻል ምን አድርገናል?

የክርስቶስ መንፈስ ያደረባቸው ሁሉ ለተቸገሩትና ከእውነተኛው መንገድ ውጭ ላሉት ሁሉ ያዝናሉ ይራራሉም፡፡ ሰውን ለመልካም ተግባር የሚቀሰቅሰውና የሚያነሳሳው ለሌሎች ማዘንና መራራት ነው፡፡  

 

 

                        ሰማያዊ መና 6

 

      እንግዲህ በጊዜው ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከኃይለኛው ከእግዚአብሔር እጅ በታች ራሳችሁን አዋርዱ፡፡1ኛ ጴጥሮስ 5፡6

 

የሰውን ሕይወት በጣም ያበላሸው የኃጢአት ሁሉ ምንጭ የሆነ ኩራት ነው፡፡ ራሳችንን ዝቅ ዝቅ ያደረግን እንደ ሆነ ይህ ኃጢአት በውስጣችን ኃይል ሊያገኝ አይችልም፡፡ ምክኒያቱም ትሑት ለሆነ ሰው እግዚአብሔር ፀጋውን በመስጠት በውስጡ ሥራውን ሊሠራ ይችላል፡፡ ከዚህም የተነሣ የትሕትና መንፈስ የጠፋበት ክርስቲያን የእግዚአብሔር ኃይልም ይጎድለዋል፡፡ በትሕትና መንፈስ የሚኖር ሰው ብቻ በክርስቶስ ፀጋ ብርቱ ሊሆን ይችላል፡፡

እንግዲህ ትሕትና የምትባለው የምታምር የመንግሥተ ሰማያት አበባ በሕይወታችን ውስጥ እያበበች እንድትኖር ምን ለማድረግ እንችላለን? የምንችለውና የሚሻለው በጌታ ፊት በንስሐ ብንወድቅና ብንፀልይ ብቻ ነው፡፡ ስንፀልይም እንዲህ እንበል፡ አምላክ ሆይ በሕይወቴ ውስጥ የትሕትናን መንፈስ የሚከለክል ነገር ምን እንደ ሆነ አሳየኝ፡፡ ይህንንም ከአሳየኸኝ በኃላ የምቃወምበትን ኃይልና እንዲሁም ለመንፈሳዊ ዕድገቴ እንቅፋት የሚሆንብኝን የኩራት ኃጢአት ምክንያትና መንገድ በመረዳት ከእነርሱም ጋር እንዳልተባበር ፀጋህን አብዛልኛ፡፡

አሸናፊዎች የምንሆነው ኃጢአትን ድል ከምናደርገው ይልቅ ኃጢአታችንን በእግዚአብሔር ፊት አምነን ለእርሱ አሳልፈን ብንሰጠው የተሻለ ነው፡፡ይህንን በሚገባ ያደረገ ክርስቲያን ራሱን ከኃያሉ ከእግዚአብሔር እጅ በታች ዝቅ አድርጎአል ማለት ነው፡፡ ስለዚህም የእግዚአብሔርንም ፀጋ ያገኛል ያን ጊዜም በትሐትና ለማደግ ይችላል ማለት ነው፡፡

ይህ ውብ የሆነውን የክርስቲያን ተግባር በሕይወታችን ውስጥ እንዲታይና እንዲገኝ እርሱ ራሱ በመንፈሱ ይርዳን፡፡ አሜን አሁን ይርዳን፡፡ 

 

 

                        ሰማያዊ መና 7

 

እናንተ ከእግ/ር ጋር ስትሆኑ እርሱ ከእናንተ ጋር ነው፡፡ 2ኛ ዜና 15፡2

 

በየጊዜው ለሚገጥመን የሕይወት እንቆቅልሽ መፍትሔው ይህ እላይ የተጠቀሰው ቃል ነው፡፡ በዚህ ቃል አማካይነት እውነተኛ ሰላምና ደስታን ማግኘት ይቻላል፡፡ እግ/ር አእኛ ጋር ለሆነ ማን ይቃወመናል?

እግ/ር ከእነማን ጋር ነው; የዚህ ጥያቄ መልሱ አጭር ነው፡፡ እግ/ር አብረውት ከሚሆኑት ጋር ነው፡፡ እግ/ር ከእኛ ጋር እንዲሆን ሁላችንም እንፈልጋለን፡፡ ነገር ግን እኛስ ከእግ/ር ጋር ለመሆን ፈቃደኞች ነን?

ፈቃዱ በምድር ላይ እንድትሆን መንግስቱም እንድትመጣ ስሙ እንድትቀደስ ኃጢአተኞችም ንስሐ ገብተው እንዲድኑ ናፍቆት አለንን?

በልባችን ውስጥ የምናደላው ለማን ነው; ለእግ/ር ነው ወይስ ለሌላ? ከሃሳባችንና ከንግግራችን ይልቅ እግ/ርን ከእኛ ጋር እንዲሆን የሚያደርገው ጠቅላላ የልባችን ዝንባሌ ነው፡፡ የልባችን ፍቅር ወደዚህ ዓለም ካዘነበለ እግ/ርን እንኳን እንደማይበጀን አድርገን እንገምተዋለን፡፡

ከእርሱ ጋር ብንሆን ግን እርሱ በሕይወትም በሞትም ጊዜ ከእኛ ጋር ይሆናል፡፡ 

 

 

                        ሰማያዊ መና 8

 

ዓይኖቼን ወደ ተራሮች አነሣለሁ ረዳቴ ከወዴት ይምጣ፤/ ረዳቴ ሰማይና ምድርን ከሠራ ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው፡፡ መዝሙር ዳዊት 121፡1-2.

 

የሰው ልጅ በኑሮ ዘመን ሁሉ የአምላኩን የእግ/ር እጅ አጥብቆ ይፈልጋል፡፡ የሰው ባሕሪው ከተፈጥሮ ደካማ ከመሆኑ የተነሣ ባለው ችግርና መከራ ሁሉ ወደ እግ/ር መጣበቅን ይመርጣል፡፡

ንጉስ ዳዊት ረዳት በመፈለግ ላይ እንዳለ ቃሉ ያመለክተናል፡፡ ለገጠመው ችግር ዓይኖቹን ወደ ተራሮች በማንሳት ረዳቴ ከወዴት ይምጣ ይላል፡፡ ነገር ግን ዓይኑ ከተነሣበት ተራሮች ላይ ከፍ ካሉት ቦታዎች ላይ ረዳት ሊገኝ እንዳልተቻለ ተመለከተ፡፡ ረዳቴ እኔ የማያቸውን የፈጠረና ሰማይና ምድርን ከሠራው ከእግ/ር ዘንድ ነው በማለት በአምላኩ ብቻ ሲታመን እናገኘዋለን፡፡

ዛሬ ወገኔ ረዳት ትፈልጋለህን; ረዳትህ ከወዴት ነው; ዓይኖችህስ ማንን እያዩ ናቸው; ከፍ ብለው በዚህ ዓለም ላይ ያሉወይም እንደ ተራሮች የጠነከሩ ድርጅቶች መታመኛና መፅናኛ ሊሆኑህ አይችሉም፡፡ ዓይኖችህ የምታያቸውን ሁሉ ወደ ፈጠረው ወደ ልዑል እግ/ር ከሆኑ ረዳትህ ወዳንተ ይመጣል፡፡

አንድ ሰው ለ38 ዓመት ሙሉ የታመመ የእግ/ርን ፈውስ ለመቀበል የተቀመጠ ነበር፡፡ ለ38 ዓመት ሙሉ የዚህ ሰው ጥያቄ ሰው የለኝም የሚል ነበር፡፡ ከዚህ የተሣ እቀድማለሁ ለመፈወስ ራሴን ለመቻል አልቻልኩም በማለት የውስጥ ብሶቱን ፍፁም ሰው ፍፁም አምላክ ለሆነው ጌታ ሆይ ውኃው በተናወጠ ጊዜ በመጠመቂያይቱ ውስጥ የሚያኖረኝ ሰው የለኝም ነገር ግን እኔ ስመጣ ሳለሁ ሌላው ቀድሞኝ ይወርዳል ብሎ በዮሐንስ ወንጌል 5፡7 ይነገረዋል፡፡

ለጥያቄ ሁሉ መልስ የሆነው ጌታ ተነሣና ሂድ በማለት በቃሉ ሲፈውሰው እናገኛለን፡፡ ወገኔ ዛሬየለኝም የምትለውን ነገር ሁሉ ለማን እየተናገርክ ነው ያለኸው; ሁሉን ሊያደርግ ወደ ሚችለው ጌታ ቀርበህ የሌለህን  የተቀደምክበትን ነገር ሁሉ ንገረው እርሱ ያስነሣሃል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ለጥያቄ ሁሉ መልስ ነው፡፡

 

 

ሰማያዊ መና 9

 

ጠቦቶቹን በክንዱ ሰብስቦ በብብቱ ይሸከማል፡፡ ኢሳያስ 40፡11

 

እንደዚህ ያሉ ግሩም ቃላት የተነገሩለት ማን ነው? መልካሙ እረኛ ነው፡፡ ጠቦቶቹን ወደ ብብቱ ለምን ከፍ ያደርጋል? ይህን የሚያደርግበትምክኒያት ልቡ ርኅሩኅ ስለ ሆነና ደካሞቹን ለመርዳት ስለሚወድ ነው፡፡ አለማወቃቸውንና ምስኪንነታቸውን ሲያይ ታናሾች በጎቹን ይንከባከባቸዋል፡፡

ታማኝ ሊቃ ካህን እንደ መሆኑ መጠን ደካማን መርዳት ተግባሩና ልማዱ ነው፡፡ ከዚህ በላይ በገዛ ደሙ የገዛቸው ንብረቱ ስለ ሆኑ በውድ የገዛቸውን ከክፉ ይጠብቃቸዋል፡፡ አንዷ ጠቦት እንኳ እንድትጠፋ አይፈልግም፡፡ከዚህም በላይ ሁሉም የክብሩና የባሕሪው ተካፋዮች ናቸው፡፡

ይሸከማል የሚለው ቃል በፈተና ጊዜ እንደሚረዳቸውና እንደሚንከባከባቸው ይገልፃል፡፡ ጠቦቶቹን በክንዱ ይሰበስባል የሚለው ቃል ደግሞ ወሰን የሌለውን ፍቅሩን ያመለክታል፡፡ ባይወዳቸው ኖሮ በክንዱ ይሰበስባቸው ነበርን? ከዚህ የበለጠ ርኀሩኅነት አይገኝም፡፡

በጌታና በደካሞች ወገኖቹ መካከል ያለውን ግንኙነት በእነዚህ ቃላት አማካኝነት ልናይ እንችላለን፡፡ በክንዱ ውስጥ እስካሉ ድረስ ማንም ሊጎዳቸው አይችልም፡፡ እነሆ በዚህ አለኝታ ፍፁም እረፍትና ፅኑ መፅናናት ይገኝበታል፡፡

 

 

                        ሰማያዊ መና 10

 

በእውኑ እግ/ር ከገነት ዛፍ ሁሉ እንዳትበሉ አዝዞአልን? ዘፍጥረት 3፡1

 

በእውኑ እግ/ር አዝዞአልን? እነዚህ ከሰይጣን የሚመነጩ ቃላቶች ናቸው፡፡ እነዚህ በፈተና መርዝ የተበረዙ ቃላት ናቸው፡፡እነዚህ ጥርጣሬን በሰው ልብ ውስጥ የሚነዙ ቃላት ናቸው፡፡

ሰይጣን በእነዚህ ቃላት ያልተፈታተነው ሰው ይገኛልን? በእውኑ እግ/ር አዝዞአልን? እግ/ር የተናገረውን እንዳይሰሙ ያዘዘውን እንዳይፈፅሙ ሰዎችን የሚያደርጋቸው ይህ በፈተና መርዝ የተመረዘውና የተበረዘው ሰይጣናዊ ጥያቄ አይደለምን? ይህን አደገኛ ጥያቄ ለመቋቋም የሚችለው እግ/ርን በፍፁም ልብ በፍፁም ነፍስ በፍፁም አይምሮ በማመንና ቃሉን በመጠበቅ ነው፡፡ ይህን የመሰለውን እምነት ያለው ሰው የእግ/ር እውነተኛነት የሰይጣን ሐሰተኝነት ምን ጊዜም ይከሰትለታል፡፡

ሰይጣን እውነትን የሚያውቅ የመሰለ ነገር ግን በውሸት የታጀበ ውሸታም ነው ወደ ስዎችም ሲቀርብም እውነት መስሎ እንጂ ውሸት መስሎ አይደለም፡፡ ለዚህም ቡዙ ሰዎች ይስቱበታል ኃላም ይፀፀቱበታል፡፡ ወገኔ ዙሪያህን ዛሬ የከበበው ምንድን ነው? እውነትን ከውሸት ለመለየት የምትችለው እንዴት ባለ መንገድ ነው? እውነተኛውና ብቸኛው መለያ መንገድ ወደ እግ/ር መቅረብ ብቻ ነው፡፡ እውነት ነኝ ያለው እርሱም በብርሃኑ የከበረውን ከተዋረደው ሊገባን በሚችል መንገድ ያሳየናል፡፡

 

 

                  ሰማያዊ መና 11

 

ከእየሱስም ጋር እንደ ነበሩ አወቃቸው፡፡ የሐዋሪያት ሥራ 4፡13

 

ክርስቲያን የሆነ ሰው ክርስቶስን መምሰል አለበት፡፡ ስለ ክርስቶስ የሕይወት ታሪክ ግሩም በሆነ አኳኋን የተፃፉ መጸሐፍት አንብበን ይሆናል፡፡ የክርስቶስ ነዋሪ የሕይወት ታሪክ ግን የምዕመናኑ ሕይወትና ሥራ ነው፡፡ መልካችን ኢየሱስን ከመምሰሉ የተነሣ ዓለም ባየን ጊዜ ያለ ጥርጥር ከእየሱስ ጋር እንደ ነበሩ አወቁአቸው እንዲሉን ፍፁም አምሳያው ለመሆን ለፍሳችን ኢየሱስን መናፈቅ አለበት፡፡

ክርስቲያን በሕይወቱና በሥራው እንደ ክርስቶስ መሆን አለበት፡፡ በሃይማኖት በፍቅሩና በመንፈሱ ጌታውን መምሰል ይገባዋል፡፡ ሰዎችም ሥራችንን አይተው ከኢየሱስ ጋር ነበሩ እንዲሉን መልካም እንስብ መልካም እንናገር መልካምም እንሥራ፡፡

ኢየሱስን በቅድስናው እንምሰለው፡፡ እርሱ ሰዎችን ለማገልገል ዝግጁ ነበር፡፡ እኛም እንደ እርሱ እንሁን፡፡ ክርስቶስ ስለ ራሱ ባለማሰብ ሁልጊዜ ራሱን ይሰዋ ነበር፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ክርስቶስን መምሰል የፈለግን እንደሆነ አባት ሆይ ይቅር በላቸው የሚያደርጉትን አያውቁትምና የሚለውን ፀሎቱን ሁልጊዜ በማስታወስ ይቅርታ ይደረግልን ዘንድ ይቅር ባይ መንፈስና ዝንባሌ እንዲኖረን ያስፈልጋል፡፡

 

 

                  ሰማያዊ መና 12

 

ወንድሞቼ ሆይ ስለ እኛ ፀልዩ፡፡ 1ኛ ተሶሎንቄ 5፡25

 

በፀሎት የሚገኘውን ድጋፍ መፈለግ በእግ/ር አገልጋዮች ዘንድ የተለመደ ነገር ነው፡፡ የጳውሎስንም ቃል የራሳቸው በማድረግ ወንድሞች ሆይ ስለ እኛ ፀልዩ በማለት የልመና ቃላቸውን ያሰሙ ብዙዎች ናቸው፡፡ ጳውሎስ ፀጋና ኃይል የተሰጠው ታላቅ ሐዋሪያ ነበር፡፡ ዳሩ ግን እርሱና የሥራ ጓደኞቹ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚከናወኑት ተግባር ለበረከት እንዲሆን በማለት ፀሎት እንዲደረግላቸው አሳሰበ፡፡ ጳውሎስ በሥራው የምዕመናን የፀሎት ድጋፍ ከአስፈለገው ዛሬ የምንገኝ የእግ/ር አገልጋዮች ሁሉ የበለጠ የምዕመናን ምልጃ የሚያስፈልገን መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡

ስለ እኛ ፀልዩ፡፡

ይህ ድምፅ ከቀሳውስት ከወንጌል መልዕክተኞች ከመምህራንና በእግ/ር ሥራ ውስጥ ድርሻና ክፍል ካላቸው አንደበት የሚመነጭ መሆኑ ተሰምቶን ያውቃልን; የክርስቶስን የደኅንነት ቃል ለአሕዛብ ለማሰማት በችግር በስቃይና በስደት ውስጥ የሚገኙ የእግ/ር አገልጋዮች አዘውትረው ስለ እኛ ፀለዩ የሚለውን ቃላቸውን ያሰማሉ፡፡

ስለዚህ ሰዎችን ወደ ክርስቶስ ለመምራት ከዚህ ዓለም ገዢ ጋር ፅኑ ተጋድሎ ለሚያደርጉት ሁሉ የልመና ዓይናችንን ወደ ጌታ በማቅናት እንፀልይላቸው፡፡ 

 

 

                      

 

ሰማያዊ መና 13

 

በመከራዬ ቀን በድንኳን ሰውሮኛልና፡፡ መዝሙር 26፡5

 

በሕይወታችን የማይዘነጋ መታሰቢያቸውንትተውልን ያለፉ ብዙ ቀኖች አሉ፡፡ ዳዊት ስለ መከራ ጊዜ ወይም ስለ ክፉ ቀን ይናገራል፡፡ ጳውሎስ በክፉው ቀን ለመቃወም እንድትችሉ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ አንሱ በማለት የኤፌሶንን ክርስቲያኖች መክሮአቸዋል፡፡ ኤፌሶን 6፡13

በእያንዳንዱ ሰው ሕይወት እላይ የተገለፀው የመከራ ቀን እንደሚደርስበት የታወቀ ነው፡፡ እያዳንዳችን ወደ ኃላ መለስ ብለን ያሳለፍነውን የሕይወት ዘመናችንን ስንመለከት እንዲህ ያለውን ክፉ ቀን አሳልፌአለሁ የምንለው ጊዜ መኖሩ አይካድም፡፡

በመከራ ጊዜ ወደ እግ/ር ድንኳን የተጠጋን ሁሉ ከተቃጣብን አደጋ ለመዳን መቻላችንን እናስታውሳለን፡፡ በሕይወታችን የሳለፍናቸው የደስታ ቀኖች መኖራቸው ጥርጥር የለውም፡፡ የእግ/ር ቅርብነት ቢሰማን ልባችን በደስታና በምስጋና ይሞላል፡፡

እግ/ር በክፉም ሆነ በደግ ቀን በድንኳን ውስጥ እንዲሰውረን የዘወትር ፀሎታችን ይህን፡፡

 

                  ሰማያዊ መና 14

 

የስንዴ ቅንጣት በምድር ወድቃ ካልሞተች ብቻዋን ትቀራለች፡፡ ዮሐንስ 12፡24

 

ይህ የኢየሱስ ቃል ወደ እግ/ር በንስሐ የተመለሱ ብዙ ሰዎች በሕይወታቸው ፍሬ የማያፍሩበትን ምክኒያት ሊያስረዳን ይችላል፡፡

አያሌ ሰዎች የአዲሱ ሕይወት ባለቤት ለመሆን ይጣጣራሉ፡፡ ከአሮጌው ኑሮአችን ጋር መሰናበትን ግን አይፈቅዱም፡፡ በሌላ አነጋገር እንደ ስንዴ ቅንጣት በምድር ላይ ወድቀው ፍሬ ማፍራት አይሆንላቸውም፡፡ አሮጌ ሰውነታቸውን ለመቋቋም ሙከራ ያደርጋሉ፡፡ ዳሩ ግን የአሮጌው ሰውነታችውን ፈቃድና ዝንባሌ ከክርስቶስ መስቀል ሥር ማዋል ይጨንቃቸዋል፡፡

ብዙ ሰዎች ያለ ፍሬ ብቻቸውን የሚቀሩት በዚህ ምክኒያት ነው፡፡ ከአሮጌው አዳም የባርነት ቀንበር ሥር እስካሉ ድረስ ሌሎችን ወደ እግ/ር መምራት ያለባቸው መሆኑ አይሰማቸውም፡፡ ሕይወታቸው እንኳን ዓለማ ያለው አይመስላቸውም፡፡

ራሳችንን ዝቅ በማድረግ መሬት ላይ በመውደቅ የአሮጌውን ሰውነታችንን ምኞትና ፍላጎት ለማሸነፍ ፍቃደኞች ከሆን ፍሬ ማፍራታችን አይቀርም፡፡

ለመንፈሳዊ ሕይወታችን መሰናክል የሚሆኑ ቅን ነገሮች ሁሉ ለእግ/ር አሳልፈን እንስጥ፡፡ እርሱም ሕይወታችንን በማደስ ፍሬ እንድናፈራ ያደርገናል፡፡

 

 

                  ሰማያዊ መና 15

 

ከእኔ ጋር ደስ ይበላችሁ፡፡ ሉቃስ 15፡6

 

የጠፋውን በጉን በማግኘቱ እረኛው ከፍ ያለ ደስታ ተሰምቶት ነበር፡፡ ደስታውም ከሌሎች ሰዎች ጋር የሚጋሩት እንጂ ለራስ ብቻ የሚያስቀሩት አልነበረም፡፡ ጎረቤቶችንና ወዳጆቹን ሁሉ ሰብስቦ ከእኔ ጋር ደስ ይበላችሁ በማለት የደስታው ተካፋይ እንዲሆኑ ጋበዛቸው፡፡

ደስታችንን ሰዎች እንዲካፈሉ እንወዳለን? ከጎረቤታችን አንዱ የጠፋበትን በግ ሲያገኝ ከእርሱ ጋር ደስ ይለናል? በሌሎች አገሮች የሚፈፀመው የወንጌል ሥራ ሲቀና ደስታ ይሰማናልን; የራሳችን ያልሆኑት አብያተ ክርስቲያናት ሥራ ሲደራጅና ሲስፋፋ ስናይስ እንደሰታለን?

እውነተኛና ቅዱስ የሆነ ደስታ ድንበርና ወሰን የለውም፡፡ ከእራሱ የእምነት ክልል ውጪ በሚገኙት ምዕመናን ጥረት ሰዎች ወደ ደኅንነት ሲመሩ ሲያይ የማይደሰት ሰው የእግ/ር መንፈስ አለው ለማለት አያስደፍርም፡፡

ጌታ እያንዳንዳችንን ከእኔ ጋር ደስ ይበላችሁ ይለናል፡፡ በማንኛውም ሥፍራ የሚገኝ ሰው በንስሐ ወደ እግ/ር ሲመለስ በሰማይ ደስታ እንደሚሆን እንውቃለን፡፡ይህን የመሰለው ደስታ በምድር ላይ እንዲኖር ያስፈልጋል፡፡

እግ/ር በምድር ላይ በሚፈፅመው ሥራ በምድር ላይ ያሉ ልጆቹ ከሰማይ መላዕክት ጋር ደስ እንዲላቸው ያስፈልጋል፡፡  

 

 

 

                  ሰማያዊ መና 16

 

                  ስለ እኔ ለምኑ ኤፌሶን 6፡19

 

ጳውሎስ ስለ እኔ ለምኑ ይላል፡፡ ምእመናን እንዲፀልዩለት የፈለገው ስለ ምንድን ነው; የወንጌል ሚስጥር በግልጥና በድፍረት እንዳስታውቅ አፌን በመክፈት ቃል ይሰጠኝ ዘንድ ስለ እኔ ለምኑ፡፡

ሐዋሪያው እንዲሰጠው የፈለገው ቃልና ድፍረትን ነበር፡፡ ስለ እነዚህ ነገሮች መፀለይ አስፈላጊ ነውን? ጳውሎስ ለቡዙዎቹም ሆነ ለጥቂት ሰዎች የወንጌልን ቃል በድፍረት በመስበክ ችሎታውን አሳይቶ አልነበረምን?

ጳውሎስ ከፍ ያለ ችሎታ የነበረው ሐዋሪያ ቢሆንም እንኳን ዕለት ዕለት አዲስ የፀጋ ረድኤት የሚያስፈልገው መሆኑን በሚገባ ተገንዝቦ ነበር፡፡ በየዕለቱ ከእግ/ር በሚሰጠን በረከትና ረድኤት መጠቀም ይገባናል፡፡ እንደ እስራኤላውያን ለየቀኑ የሚያበቃን መና ማለዳ ተነስተን መሰብሰብ ይኖርብናል፡፡

በሕይወታችን ዘመን ለምንወስደው ለእያንዳንዱ እርምጃ የሚረዳን ኃይልና ፀጋ ከእግ/ር ዘንድ ማግኘት ያስፈልገናል፡፡ ምዕመናን ወንድሞቻችንም በፀሎት ክንዳቸው እንዲሸከሙን ስለ እኔ ለምኑ ማለትን መዘንጋት አያሻም፡፡

እግ/ር በየዕለቱ የሚያስፈልገንን ፀጋና ረድኤት ሊሰጠን ዝግጁ ነው፡፡ የእግ/ር ቃል እንደሚነግረን ሁሉ የእግ/ር ቸርነት ማለዳ ማለዳ አዲስ ነው፡፡ ሰቆቃው ኤርሚያስ 3፡23 ቸር ነውና ምህረቱ ለዘላለም ነውና እግ/ርን አመስግኑ፡፡ መዝሙር 107፡1